Você está na página 1de 4

ደቡብና የፖለቲካ አቅጣጫው። (ክፍል 1)

("ቀጣዩ ስራ ምን ሊሆን ይገባል?"-- የግል አስተያየት።)

ደቡብ ኢትዮጵያ እንደቁመቱ ችግሩ የሰፋና እንደአተጫጨቁ ውስብስብ እየሆነ ያለ የኢትዮጵያ ክፍል
ሆኗል። ከስሙ ጀምሮ ግራ የሚያጋባው ይህ አካባቢ በቀደመው የኢህአዴግ አስተዳደር የተዳደረበት አሰራር
ነዋሪዎቹን እርስበርስ እንዳይተማመኑ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ስለዚህ ጉዳይ ተደጋግሞ የተፃፈና የተነገረ
በመሆኑ በዚህ ፅሁፍ የሚነሳው ሀሳብ በድፍን ስለተተወውና `ለኮፍ` ከማድረግ ያለፈ ሁሉም ደፍሮ
ስላልተናገረው ቀጣዩ የፖለቲካ አቅጣጫ ነው።

በልማድ "ደቡብ" በመባል የሚታወቀው የማህበረሰብ ክፍል መካከለኛው ደቡብ ምእራብን÷ ደቡብ
ምእራቡንና የመካከለኛውን ደቡብ ኢትዮጵያን የሚያካትተው የኢህአዴጉ "የደቡብ ብሄሮች÷ ብሄረሰቦችና
ህዝቦች" ክልል ነው። በኢህአዴግ ቋንቋ የክልሉ ስያሜ በራሱ ከፋፍሎ ግን አጭቆ ለማስቀመጥና የእርስበርስ
ግጭቱንና የውስጥ ውስጡን ክፍፍል ለማዝለቅ የተሰጠ እንደሆነ ግልፅ ነው። በዚህ ስሌትም ላለፈው ሩብ
ምእተዓመት ሌላውን የሚጠቅምና አካባቢውን የበለጠ እርስበርስ የሚከፋፍል የፖለቲካ ስራ
ተሰርቶበታል። ዛሬስ "በተለወጠው" የኢህአዴግ አጀንዳ የደቡብ ህዝብ ምን አስቧል? "ለማሰብ"
ያልተፈጠረው ደኢህዴኑ ምን ታስቦለታል? በወያኔ በተቀደደለትና በተደከመለት ቦይ ፈስሶ ክፍፍሉን
አጠናክሮ ይዘልቃል ወይስ በጅምላ ታጭቆ እንደተተወው ከሰሜንም ሆነ ከሌላው የአገሪቱ ጥግ የመጣው
ሁሉ "ገዢና ብልጣብልጥ" መጫወቻ ሆኖ ይቀጥላል?

ራሳቸውን በብሔር አደራጅተው "የደቡብ ክልል በብሄር ተከፋፍሎ ክልሉ ቢበዛና ቢዋቀር ይበጣጠሳል"
በሚል መሞከሪያነቱን ታጭቆ እንዲቀጥል ከሚያልመው ኢህአዴግ አንስቶ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያየ
አይነት ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች እንዳሉ ግልፅ ነው። ከኢህአዴጉ ደኢህዴን ሌላ ከመሀል ሰፋሪው
የመድረክ ክንፍ ጀምሮ "የዜግነት ፖለቲካ" እስከሚሉት÷ እንዲሁም በየትም ተብሎ "ለመኖ ከሚሆን"
ስልጣን ውጭ ለክልሉ በሚረባው ጉዳይ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ የሌላቸው ፓርቲዎችና የፖለቲካ ዝንባሌዎች
ሁሉ ይስተዋላሉ።

ሁሉም በሚያዋጣው እየተደራጀ የሚፈልገውን ርእዮት ማጠናከር መብቱ ቢሆንም÷ አሁን ካለው የአገሪቱ
የፖለቲካ ዝንባሌና አዝማሚያ አንፃር "የደቡቡ ህዝብ የሚመጥነውን ፓርቲ አላገኘም" የሚሉ ብዙዎች
ናቸው። ይህንን አባባል ተከትሎ ካስተዋልኩትና የተለያዩ ወገኖችን በማነጋገር እንደተረዳሁት የአብዛኞቹ
አስተያየት ሰጪዎች ድምዳሜ ከሁለት ምክንያቶች በመነሳት ይመስለኛል። ከምክንያቶቹ አንዱ ያሉት
ተፎካካሪ ፖለቲከኞች እንቅስቃሴና ዝንባሌ የደቡብን ህዝብ ችግር የማይፈታ መሆኑ ሲሆን ሌላኛው
ምክንያት ደግሞ በትምህርትም ሆነ በእድሜ የበሰሉት አብዛኞቹ የክልሉ ሰዎች ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ
ያላቸው ስሜት "በመጠረዝ÷ በመደንዘዝ አሊያም በመጠለዝ" አስተያየት የተቃኘ በመሆኑ ነው ማለት
ይቻላል።

እነዚህ ሁለት ምክንያቶች አሁን ባሉት "ፖለቲከኞችና ለፖለቲካው መዛነፍ ምክንያት ከሆኑት በፖለቲካው
በቀጥታ የማይሳተፉ ነገር ግን ተፅእኖ በሚፈጥሩ ወገኖች" ተሳትፎ ጭምር የተከሰቱ መሆናቸው መታወቅ
አለበት። ከዚህ ሌላ÷ የራሱ የክልሉ ተጨባጭ ሁኔታና ቅርፅ የሚያሳድረው ውስጣዊ አሉታዊ ተፅእኖ ሳያንስ
ተጨማሪ ውጫዊ አባባሽ ሁኔታዎችም አይጠፉም። ይኸው የክልሉ መልክ ግራ በተጋባ መልኩ
እንዳይቀጥል÷ ህብረተሰቡም የራሱን አማራጭ በሰከነ መንገድ እንዲያፈላልግ በማድረግ በኩል ሚዲያ
የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህ መሰረት በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው የተጀመሩትና የህዝቡን
ድምፅ በማስተጋባት እውነተኛ የሆኑት ድምፆች መጠናከራቸው የግድ አስፈላጊ ነው። በአንፃሩ ደግሞ
በሚዲያ ስም የተወሰነ የፖለቲካ አላማ ይዘው በጅምላ አስተሳሰብ "ሁሉንም ለመበየን" የሚጥሩ
አካላትም መከሰታቸውን ማስተዋል መልካም ነው። በተለይም በሚዲያ ስም የተለቀቀ ግን የተለያዩ ግቦችን
በመያዝ የሚንሳፈፍ አካልም እንዳለ ማወቁ ተገቢ ነው። በመንግስትነት በሞኖፖል የክልሉን የህዝብ ሚዲያ
ከሚያዘው ደኢህዴን ሌላ "የግንቦት ሰባትን ተልእኮ ለማሳካት የታለመ" ነው የሚባል አቀንቃኝ ሚዲያም
ይታወቃል። "የሶሻል ዴሞክራቱን ፓርቲ ሀሳቦች ለማወደስና ተፎካካሪዎቹን ለመኮነን የሚሰራ" ይኸ ነው
የሚባል ክፍል ባይኖርም በየራሳቸው ፍላጎት የየወጡበትን ማህበረሰብ ፍላጎትና መብት በሚመለከት ብቅ
ብቅ ያሉ ገፆችም አልጠፉም።

ለዲሞክራሲው ተሳትፎም ሆነ ሀሳብን ለማንሸራሸር የሚዲያዎቹ መጠናከር የሚፈለግ እንደመሆኑ


ሊበረታቱ ይገባል። በአንፃሩ ትክክለኛ መልኩን ይኸ ነው ለማለት ቢያስቸግርም÷ "ደቡብ" በሚባለው ክልል
በኢህአዴግ በደረሰባቸው ግፍ የተማረሩና ህገመንግሰቱን መሰረት አድርጎ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት
የሚጠይቁትን ሁሉ በጭፍን "እንደከፋፋይ" በመቁጠር ያንን ሀሳብ የሚያራምድን ሁሉ የሚቃወም
ሚዲያም አይጠፋም። እንደሚዲያም ሆነ እንደአካባቢው ተቆርቋሪ የቆመለትን አላማ መሰረት አድርጎ
ማንም ያሻውን የማራመድ መብቱ የተጠበቀና ተቀባይነት ያለው ነው። ሁሉንም ሰብስቦ "በዚህ መንገድ
ካልሄድን" በሚል ሌት ተቀን የሚተጋውን ግን "በቃህ" ማለትም ተገቢ ይሆናል። በዚህ መልኩም
ዴሞክራሲን መለማመዱም ሆነ ለውጡን ማጠናከሩ ይቀጥላል።

ከፖለቲካው አኳያ አሁንም የ"ደቡብ ኢትዮጵያ"ን ድምፅ አመጣጥኖ የሚያሰማና ከምር የሆነ አጀንዳ ይዞና
ያለበትን ሁኔታ ተረድቶ÷ ፖሊሲ ቀርፆ ሊመራው የተዘጋጀ ድርጅት ያገኘ አይመስለኝም። ሁሉም ለጥቅሙ
በሚዘውረው ፖለቲካ አጃቢ ከመሆን ባለፈ የአካባቢው ህዝብ የራሱን መብት ሊያስከብርለት የሚችል÷
ዘመኑን ያገናዘበና በመርህ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ አሁንም አላገኘም። ለዚህ ከፍተኛ እድል የነበረውና
በተደራጀ መልኩ የተሻለ አጋጣሚ የተቸረው የኢህአዴጉ ደኢህዴን ቢሆንም ባለመለወጡና ከስህተቱ
ተምሮ መሻሻሉን ባለማሳየቱ አልተሳካለትም። ራሱን ተኩሶ ባይገድልም ለመምራት በማይችል መልኩ
እውር ድንብሩን በመጓዝ ራሱን ክፉኛ አቁስሏል።

ከኢህአዴጉ ደኢህዴን ውጪ እንደአማራጭ ለመታየት እድል የነበረው የፕሮፌሰር በየነ "ሶሻል ዴሞክራት"
ነኝ የሚለው ፓርቲም የስሙን ያህል ያማረ ይዞታ አለው ለማለት ይከብዳል። "ፓርቲው" ላለፉት 27
ዓመታት ከሚመሩት ሰው ጋር ስሙን እየቀያየረና ከመጣው ሁሉ ጋር እየተዳበለ ከመጠራት በዘለለ ይኸ
ነው የሚባል መሰረት ያለው ስለመሆኑ የሚከራከሩት ብዙ ናቸው። በፓርቲ ደረጃ ተሰባስቦ የደቡብን ክልል
ሁሉንም ወገኖች ባካተተና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መሪዎቹን ሲመርጥም ሆነ ፖሊሲውን
ሲያስተዋውቅ ብዙም አለመስተዋሉ በዚህ በኩል የጎዳው ይመስለኛል። ከዚህ ውጪ የደቡብን ክልል ባህርይ
ያላገናዘበ ካርታ ይዞ ጥቂት ከተሜዎችን ባማከለ አሰራር የሚንቀሳቀሰው "ግንቦት ሰባት" የሚባለው
ድርጅትም ከህዝቡ ቀልብ የገባ አይመስልም። ለአማራና ለኦሮሚያ ክልሎች ያለውን ፍቅር የሚያጎላው
የግንባሩ ሚዲያም ከደቡብ አንፃር ብዙም ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሌለው በተደጋጋሚ ለማሳየት
ሞክሯል። ከዚህ አንፃር ፓርቲው ለደቡብ÷ በተለይም ለገጠሩና ታጭቆ ለሚገዛውና አካባቢውን
ለማሳደግና ቋንቋና ባህሉን ለማጠናከር ለሚፈልገው ክፍል ብዙም አጀንዳ እንደሌለው ይታማል ። ስለዚህ
እነዚህ የተጠቀሱት የፖለቲካ ድርጅቶች በአካባቢው ተመራጭ ለመሆን ካሻቸው ችግሮቻቸውን
አስተካክለው ተመራጭ ለመሆን ራሳቸውን አዘጋጅተው ለመቅረብ መጣር ይኖርባቸዋል።
"ደቡብ ኢትዮጵያ" የራሱን አጀንዳ የሚያራምዱና ህዝቡን የሚረዱ÷ የክልሉን ተጨባጭ ሁኔታ የተገነዘቡና
ለሁሉም በተቻለ መጠን እኩል የሚያስቡ ሰዎችን የያዘ የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋል። ቀደም ሲል
እንደጠቆምኩት አሁን በፖለቲካው አካባቢ ውር ውር የሚለውና በእውቀትም ሆነ በእድሜ በሁለተኛው
ትውልድ ዘመን ውስጥ ያለው የንኡስ ከበርቴው ክፍል "የተጠረዘ÷ የደነዘዘ÷ አሊያም የተጠለዘ" ነው
የሚባልበትን ምክንያት እዚህ ላይ በጥቂቱ ማብራራቱ አስፈላጊ ነው። "መጠረዙ" የሚያሳየው÷
በኢህአዴግ ውስጥ ወድዶና አላማውን ፈቅዶ ገብቶ ሳይሆን ለጥቅሙና ለሆዱ ሲል የታቀፈውን÷
የማያምንበትን ፖለቲካ ለማራመድ ውስጡ እምቢ እያለው ለሆዱና ለምቾት ሲል ህሊናውን ሽጦ የገዛ
ወገኖቹን ጭምር በሚያስጠቃ ውሳኔ ጭምር የሚሳተፈውን ነው። "የደነዘዘው" የተባለው በህይወት
አጋጣሚ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን ካለፈበት የኑሮ ገፅታና በሀገሪቱ ካስተዋለው ሁኔታ የገባው ነገር
"የፖለቲካን እርኩስነትና የግፈኞች መሰባሰቢያ" መሆኑን ብቻ እንደሆነ የተረዳው ነው። በዚህ ክንፍ ያለው
ማህበረሰብ የተማረው ጭምር ከመሳተፍ ይልቅ በቸልታ የሚያሳልፍና ከትግል ይልቅ እድል የሚል÷ ማንም
ቢመጣና ቢሄድ የማይጨንቀውና ለሚገዛው ሁሉ ለመገዛትና ተመሳስሎ ለመኖር የወሰነ ነው።
"የተጠለዘው" ሁለት አይነት ነው። አንዱ በአመለካከቱ በነፃነት መኖር አቅቶት በገዢዎች ተንገላቶና
ተሰቃይቶ ከፖለቲካ ራሱን እንዲያገል ወይም ደግሞ እንዲሰደድ የተገደደው ነው። ሌላኛው "ተጠላዥ"
ደግሞ በገዢዎች ተመልምሎ በቀጥታ በፖለቲከኛነት ባይሳተፍም በአጃቢነት ኑሮውን ያመቻቸውና
በጥቅም የተሳሰረው የንኡስ ከበርቴው ክፍል ነው። የዚህኛው ቡድን ክፋት ገዢዎች ለሰሩት ለጥፋትና ግፍ
ተጠያቂ እንዳይሆኑ ለመከላከል በአስረጂነት እየቀረበ÷ "እውቀቱን በማዛባት እየተጠቀመ" በምላሹ
በሚያገኘው ዳረጎት ማህበረሰቡን መበደሉ ነው።

ከሞላ ጎደል ከላይ ባየነው ምክንያት የደቡብ ክልል ህዝብ የሚወክለውንና የሚመጥነውን ፓርቲ ያገኘ
አይመስለኝም። በዚያው አንፃር ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር አሁን ያለው የክልሉ ሁኔታ ወደመከፋፈል
እያዘነበለ ነው። በተለይ "ክልል እንሁን" በሚል የጠየቁት ዞኖች መሰረታዊ የመልማትና ፍትህ የማግኘት
ጥያቄን ካሉት ፓርቲዎች እንደአጀንዳ የሚያቀነቀን ባለመኖሩ÷ ለዚህ ምላሽ የሚታገል የህዝቡን ፍላጎትና
የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ÷ ሚዛናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብን የሚያራምድ ድርጅት ያስፈልገዋል።

"ደቡባዊ ርእዮት" ያለው ድርጅት እንዴት ሊመሰረት ይችላል? የደቡቡን ህዝብ አንድነት ጠብቆና በሌላው
የአገሪቱ ክፍል ያሉትን "ትላልቅ" ብሄረሰቦች ፍላጎትና ተፅእኖን ተቋቁሞ መዝለቅ የሚችል እውነተኛ ፓርቲ
እንዴት ማግኘት ይቻላል? በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን።

ቸር እንሁን።
መንቾ ከም (ጥር 11 ቀን 2011 ዓ•ም)

እግዚአብሄርን መምሰል
20Peter Eyakem and 19 others
9 Comments6 Shares
Like

Você também pode gostar